በህጻናት የአዕምሮ ጤና ችግር በሆነው ትኩረት የማጣት/ ADHD/ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኝት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን የሰጡት የኢትዮጵያ የካንሰር አሶሴሽን የቦርድ አባል የሆኑት ወ/ሮ ወንጌል መስፍን እንደገለጹት ትኩረት የማጣት ችግር /ADHD/ በዘር፣ በአንጎል ጉዳት፣ በእርግዝና ወቅት በሚፈጠሩ ችግሮች ፣ በከባድ ጭንቀት እና እናት በተለያዩ ሱሶች ከተጠቃች ሊከሰት የሚችል የአዕምሮ ህመም መሆኑን ገልጸው፤ ትኩረት የማጣት ችግር / ADHD/ ያለባቸው ህጻናት የቀን ቅዥት የሚያጠቃቸው፣ብዙ ነገሮችን የሚረሱ፣ ግደሌሽነት የሚስተዋልባቸው፣ አንድ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ የማይችሉ፣ ብዙ የሚያወሩ እና ተረጋግተው መቀመጥ የማይችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡ በዚህ የአዕምሮ ህመም የተጠቁ ህፃናት ወላጆች ችግሩን አምነው ለመቀበል እና በሌሎች እንዲታወቅባቸው ስለማይፈልጉ ህመሙ የሚያስከትለው ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግር ጎልቶ እንዳይታይ እና በተለምዶ ሞልቃቃ የሚባሉ ልጆች የሚያሳዩት ባህሪ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ እና ስር የሰደደ ችግር ሆኖ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል ያሉት ወ/ሮ ወንጌል ችግሩ ያለባቸው ልጆች ለከፋ ስነልቦናዊ ጫና እየተጋለጡ በመሆኑ ለህመሙ በቂ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የህመሙ ምልክት የሚታይባቸው ህጻናትን በቶሎ ወደ ጤና ተቋማት በመውሰድ ህክምና እንዲያገኙ ማደረግ፤ በችግሩ ለተጠቁ ወላጆች እና መምህራኖቻቸው በህጻናቱ እንክብካቤ ዙሪያ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ችግሩ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የመፍትሄ እርምጃ መሆኑን ወ/ሮ ወንጌል አብራርተዋል፡፡