የዓለም ኤድስ ቀን እና የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በባለሥልጣኑ ተከበረ
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ ”የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች .አይ. ቪ መከላከል!”በሚል መሪ ሐሳብ የዓለም ኤድስ ቀን እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ለ32ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ "መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ጾታዊ ጥቃትን ዝም አንበል!”በሚል መሪ ሐሳብ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ወይም የነጭ ሪቫን ቀን በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በተከበረውን በዓል ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባለሥልጣኑ የእውቅና እና ስታንዳርዳይዜሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ እንዳሉት ጾታዊ ጥቃትን ጥቃትን መጸየፍ ፣ መከላከል እና ማስቆም የኤች አይ ቪ ስርጭትን ለመግታት እና የኤች. አይ.ቪ /ኤድስ ዛሬም በማህበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን የጤና፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቀነስ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የኤች. አይ. ቪ /ኤድስ ቫይረስ ሥርጭት ዙሪያ የሚደረገውን የግንዛቤ ፈጠራ ስራ በማጠናከር እና የፈቃደኝነት የኤች. አይ. ቪ /ኤድስ ምርመራ አገልግሎትን በማስፋት ሀገራችን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 የኤች. አይ. ቪ /ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረስ የሰነቀችውን ራዕይ እውን ለማድረግ የሚደረገውን ርብርብ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሴቶች እና በህጻናት ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃትን ማስቆም የሁሉም አካላት ኃላፊነት ነው ያሉት ዶ/ር ድንኳና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለጉዳዩ በቂ ትኩረት በመስጠት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ እለቱን በማስመልከት ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ ያቀረቡት በባለሥልጣኑ የሴቶች ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ኤልሳ ይርጉ የፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድሀኒት አገልግሎቶች ፣ ሁሉ አቀፍ ተደራሽነትና ሽፋን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስና የስርጭት መጠኑን ከነበረበት ከፍተኛ መጠን ወዳለበት 0.91% ማድረስ በመቻሉ ሊያስከትል የነበረውን የከፋ ችግር ለመቀልበስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡የቫይረሱ ስርጭት ከማህበረሰብ ማህበረሰብ እንደሚለያይ የገለጹት ወ/ሪት ኤልሳ በተለይ ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ጾታዊ ጥቃት በሴቶች እና ህጻናት ላይ ከሚያስከትለው አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነልቦናዊ ተጽዕኖ በተጨማሪ ለኤች. አይ. ቪ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ እንደሚያደርግ የገለጹት ወ/ሪት ኤልሳ ጾታዊ ጥቃት የሰውን ጾታ መሠረት ያደረገ ጥቃት ነው ። በዓለም ከሶስት ሴቶች አንዷ በህይወቷ ውስጥ ጾታዊ ጥቃት ያጋጥማታል። በኢትዮጵያ ውስጥ በ2016 ዓ.ም በተካሄደው የስነ- ህዝብና ጤና ዳሰሳ በተመሳሳይ ከአራት ሴቶች ውስጥ አንዷ ከ15 አመቷ ጀምሮ ጾታዊ ጥቃት ያጋጥማታል ብለዋል። የቀረበውን የመወያያ ጽሁፍ መሠረት በማድረገው የተለያዩ አስተያየቶች እና ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፤ ለተነሱት አስተያየት እና ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል ፡፡