20ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በባለሥልጣኑ ተከበረ
"ሙስና የጋራ ጠላታችን ነዉ ፤ በሕብረት እንታገል! ” በሚል መሪ ሐሳብ በባለሥልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ህዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም በተከበረውን በዓል ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባለሥልጣኑ የእውቅና እና ስታንዳርዳይዜሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ እንዳሉት ሙስና የተሰጠ ኃላፊነትን ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ስርዓትን፣ ህግን፣ ደንብን እና የአሰራር መርሆችን የመጣስ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ ይህ አስከፊ ተግባር በሀገራችን እያስከተለ ያለው ዘርፍ ብዙ ችግር ሁሉንም የሚነካ የጋራ ጠላት በመሆኑ ይህንን ጠላት በጋራ ልንከላከለው ይገባል ብለዋል ፡፡ በባለስልጣኑ የሥነ ምግባር እና የጸረ- ሙስና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ የኔሁን ተወለ ለሙስና መከሰት የተለያዩ መንስኤዎች ቢኖሩም ከዋና ዋና ምክንያቶች መካከል አንዱ የሥነምግባር ውድቀት ዋነኛው ቢሆንም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ተቋማዊ ምክንያቶች ለችግሩ መከሰት ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ሙስና በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ከባቢያዊ ጉዳቶች እያስከተለ ይገኛል ያሉት አቶ የኔሁን የ2015 ዓ.ም የብሔራዊ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በተደረጉ የምርመራ እና የክስ ሥራዎች የብር 2,344,225,034.00 እና በዓይነት የ50,007 ካሬ ሜትር የህዝብ እና የመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት መድረሱ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች ሁሉም ሴክተሮች የስጋት ደረጃቸውና ዓይታቸው ይለያይ እንጂ ለሙስና ተጋላጭ መሆናቸውን የገለጹት አቶ የኔሁን ዋነኞቹ የግዥ ስርዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የግብር አሰባሰብና አወሳሰን ስርዓት፣ የመድሃኒት ግዥና ስርጭት፣ የትምህርት ማስረጃና ፈቃድ አሰጣጥ፣ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር፣ የገቢና ወጪ እቃዎች የዋጋ ትመናና ቀረጥ አወሳሰን፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት፣ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት፣ የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት፣ የታራሚዎች አያያዝና አስተዳደር፣ የክስ አመራር፣ የማዳበሪያ ግዥና ስርጭት፣ የጉዞ ሰነዶች አሰጣጥ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና ስምሪት፣ የከበሩ ማእድናት ቁጥጥርና አስተዳደር፣ የብድር አሰጣጥና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር፣ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትና ስርጭት፣ የንብረት አስተዳደርና አወጋገድ እንዲሁም የግንባታ አስተዳደር ላይ የሙስና ስጋቶች እንደሚታዩ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመለክቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከትምህርት ማስረጃና ፈቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያለውን የሙስና ተጋላጭነት ሥጋት ለመቀነስ እና ለመከላከል የባለሥልጣኑ ሁሉም የሥራ ክፍሎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ሊኖራቸው የሚገባ መሆኑን አቶ የኔሁን አመልክተዋል፡፡ በሥራ አስፈጻሚው የቀረበውን የውይይት መነሻ ሐሳብ መሠረት በማድረግ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው በአቶ የኔሁን ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል ፡፡